ወላይታ ልማት ማህበር በFarms for the Future ፕሮጀክት ለአርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እና በድህረ ምርት አያያዝ ላይ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ሰጠ

ወላይታ ልማት ማህበር ከጣሊያን መንግስት ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከCEFA ጋር በመተባበር በሚተገብረው Farms for the Future ፕሮጀክት አማካኝነት በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ለአርሶ አደሮች በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና አስተዳደር እንዲሁም በድህረ ምርት አያያዝና አስተዳደር ዙሪያ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና ሰጥቷል።

በስልጠናው መልዕክት ያስተላለፉት የኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ዋኬ ወላይታ ልማት ማህበር የሚያከናውናቸው የልማት ተግባራት አርሶ አደሮች ከተረጂነት ተላቅቀው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያደርጉ በመሆናቸው አርሶ አደሮች ከዚሁ ስልጠና በሚያገኙት ክህሎት ኑሮአቸውን ለማሻሻል እንዲተጉ አደራ ብለዋል፡፡ ዋና አስተዳዳሪው ጨምረውም ተሳታፊ አርሶ አደሮች በስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተግባር በመተግበር በእርሻዎቻቸው ውጤታማ ሥራዎችን እንዲያከናውኑ፣ የተማሩትንም ለሌሎች አርሶ አደሮች በማካፈል የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያፋጥኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የFarms for the Future ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዳንኤል ባልጣ በሰጡት አስተያየት፣ የስልጠናው ዋና ዓላማ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የአትክልትና ፍራፍሬ አመራረት ቴክኒኮችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ የድህረ ምርት ብክነትን በመቀነስ የምርት ጥራትና የገበያ ተወዳዳሪነት እንዲያጎለብቱ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የተሰጠው ስልጠና በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይወሰን ከተግባራዊ ልምምድ ጋር በመያያዝ በግብርና ላይ ለውጥ እንዲያመጣ መታቀዱን ጠቅሰው፣ አርሶ አደሮቹ ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በተግባር በመተግበር ለራሳቸውና ለአካባቢያቸው አርአያ እንዲሆኑ አሳስበዋል። እንዲሁም ወላይታ ልማት ማህበር ከአጋር ተቋማት ጋር በመተባበር አርሶ አደሮችን በቴክኒክ፣ በግብዓት እና በተከታታይ የሙያ ድጋፍ በማገዝ ዘላቂ የግብርና ልማትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው ብለዋል።

ስልጠናውን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጉድኝት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና ተመራማሪ ዶ/ር አብርሃም ሹምቡሎ የሰጡ ሲሆን በስልጠናው አርሶ አደሮች የአትክልትና ፍራፍሬ ሰብሎችን በዘመናዊ የግብርና ቴክኒኮች ማምረት፣ የተሻሻሉ ዘሮችን መጠቀም፣ የተባይና የበሽታ መከላከል እንዲሁም የሰብል አስተዳደር ዘዴዎችን በተግባር ተለማምደዋል። በተጨማሪም ምርት ከተሰበሰበ በኋላ የሚከናወኑ የመለየት፣ የማከማቸት፣ የማጓጓዝ እና ለገበያ የማቅረብ ዘዴዎች ላይ የተግባር ልምምድ አግኝተዋል።

ወላይታ ልማት ማህበር በFarms for the Future ፕሮጀክት አማካኝነት የአርሶ አደሮችን የማምረት አቅም፣ የገበያ ተወዳዳሪነት እና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚያግዙ የአቅም ግንባታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል::