ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ሕፃናትን ወደ ትምህርት ለመመለስ፣ የትምህርት ዕድልን ለማስፋትና የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ሉሚኖስ ፈንድ ኢትዮጵያ ከወላይታ ልማት ማህበር፣ ከወላይታ ዞንና ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ጋር ያለውን ትብብር በቀጣይ ለማጠናከር ያለመ ምክክር አካሄደ።



የሉሚኖስ ፈንድ ፕሮግራም ሲኒየር ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ገብረ፥ በረጅም ጊዜ ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር በተገነባዉ አጋርነት በተፋጠነ ትምህርት መርሀ ግብር ዉጤታማ ስራ መሰራቱን በማስታወስ ለበለጠ ዉጤታማነት ከአካባቢው ትምህርት መዋቅሮችና ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር ያለው ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ በበኩላቸዉ፥ ልማት ማህበሩ ለትምህርት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታዉሰዉ ከሉሚኖስ ፈንድ ጋር በአጋርነት የሚሰራዉ ስራ እንደወላይታ በተለይም የህጻናት ፍልሰትና ከትምህርት ገበታ ማቋረጥ ዓይነት ተግዳሮት ባለበት ወሳኝ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ሳኦል፥ ሉሚኖስ ፈንድ በወላይታ የትምህርት እድል ያጡ ህፃናትን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው በማለት ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ በዞን ደረጃ በቁርጠኝነት የምንከታተለውና አስፈላጊውን ሙያዊና አስተዳደራዊ እገዛ የምናደርግ ይሆናል ብለዋል።



የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይና የመምሪያዉ ምክትል ኃላፊ አቶ ለዉጡ ሎሃ፥ በሉሚኖስ ፈንድና በልማት ማህበሩ የተጀመሩ የተፋጠነ ትምህርት መርሀ ግብርና የዳግም ዕድል ትምህርት ተግባራትን አጠናክረዉ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ውይይቱ በቀጣይ በትምህርት ዘርፉ በተለይም በዳግም ዕድል ትምህርትና በመንግስት የሚተገበር የተፋጠነ ትምህርት መርሀግብርን በጋራ ለመምራትና ውጤታማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ተጠናቋል።


