ማህበሩ ባዘጋጀው በዚህ የልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ እራት ግብዣ መርሀ ግብር የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ የወላይታ ዞንና ወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ፣ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ ባለሀብቶች፣ የማህበሩ አባላት እና የአካባቢው ታዋቂ እንግዶች ተገኝተዋል።



መርሀ ግብሩ በወላይታ ልማት ማህበር እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የተዘጋጀ ሲሆን፣ በተለይም በሰዉ ሀብት ልማት፣ በዘላቂ ኑሮ ማሻሻያና በተቀናጀ ጤና ዘርፎች የተከናወኑ ስራዎች በሰፊው በመተግበር ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ ተብራርቷል።
በዚሁ ወቅት የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዉ ክቡር አቶ ገብረመስቀል ጫላ ባደረጉት ንግግር ልማት ማህበራችንን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ እንስራ ብለዋል። ጨምረዉም የወላይታ ልማት ማህበር ለህዝቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዘላቂ የገቢ ምንጭ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፣ የተጀመረው የልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ማህበሩ ወደ ተሻለ የአገልግሎት ደረጃ እንዲሸጋገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ በበኩላቸዉ ማህበሩ ከአባላቱና ከደጋፊዎቹ ጋር በመተባበር የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በጀመረዉ ልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም የተሳተፉ አካላትን በማመስገን በተሰበሰበው ሀብት ተጀምረዉ ያልተጠናቀቁ እና አዳዲስ ስራዎች እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በእራት ግብዣው ላይ የተገኙ እንግዶችም ማህበሩ እያከናወነ ላለው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የማያደርጉ የልማት ስራዎች ላይ ያላቸውን አዎንታዊ አስተያየቶች በመግለፅ በቀጣይም ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
በመጨረሻም በመርሀ ግብሩ ላይ ለተገኙ እንግዶች፣ ደጋፊዎች እና አጋር ተቋማት የምስጋና መልዕክት በስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዉ በአቶ ገብረመስቀል ጫላ የተላለፈ ሲሆን፣ ማህበሩ በቀጣይም ለህብረተሰቡ ጠቃሚ የሆኑ የልማት ስራዎችን በስፋት ለማከናወን እንደሚቀጥል ተገልጿል።





