በዛሬዉ ዕለት በኬንያ የሚኖሩ ከ500 በላይ የወላይታ ተወላጆችና ወዳጆች በአንድነት ተሰብስበው የወላይታ ልማት ማህበር ኬንያ ቅርንጫፍ በይፋ አቋቁመዋል። የቅርጫፉ ምስረታ የተካሄደዉ በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲሆን ቅርንጫፉን ለአንድ ዓመት የሚያስተባብሩ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፤ በመተዳደሪያ ደንብ ላይ ዉይይት ተደርጎም ጸድቋል።
በምስረታዉ ስነ-ስርዓት በኬንያ የኢፌዴሪ አምባሳደር ክቡር አምባሳደር ባጫ ደበሌ እና የሚስዮኑ ምክትል መሪ አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ ተገኝተዉ መድረኩን ከወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ ጋር በጋራ በመሆን መርተዋል፤ ንግግርም አድርገዋል።



በምስረታዉ ስነ-ስርዓት ላይ የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበባዬሁ ቶራ የተገኙ ሲሆን ዶ/ር አበባዬሁ በንግግራቸው የኬንያ ቅርንጫፍ መመስረት በውጭ ሀገር ያሉ ወገኖች በወላይታ ልማት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክር እና ማህበሩ በሚያከናዉናቸዉ በትምህርት፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት እና በማህበራዊ ዘርፎች የሚካሄዱ ተግባራትን ለመደገፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።





