የወላይታ ልማት ማህበር በልማት ተግባራቱ ዜጎች እንዲሳተፉ የስራ አካባቢያቸው ለስራ ምቹ እንዲሆን ከአጋር ድርጅቶችና ከመንግስት ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ ማህበሩ በራሱ የጥቃት ጥበቃ ፖሊሲ ያለው ሲሆን ባለድርሻ አካላትንም ስለፖሊሲው ለማሳወቅ ስልጠናዎችንና የግንዘቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እያመቻቸ አወንታዊ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡
ማህበሩ በዛሬው ዕለት ስለጥቃት ጥበቃ ፖሊሲ ፍሬምወርክና አካል ጉዳተኞችን ስለማካተት ከዳሞት ሶሬ፣ ዳሞት ጋሌ እና ዳሞት ወይዴ ወረዳዎች ለተወጣጡ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል፡፡ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ልማት ማህበሩ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በሁለንተናዊ ዕድገት እንደሚሰራ በመናገር በዚህም የያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ አቶ አሰፋ ጨምረውም የጥቃት ጥበቃ ፖሊሲ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በልማት ስራ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻች ተናረዋል፡፡
በወላይታ ልማት ማህበር የጥቃት ጥበቃ ፎካል የሆኑት አቶ እንዳለማው ታፈሰ ስለጥቃት ጥበቃ ፖሊሲና አካ ጉዳተኞችን ስለማካተት ለመድረኩ ተሳታፊዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ወደየመጡበት መዋቅሮች በሚመለሱበት ወቅት ለፖሊሲው ተግባራዊነት ከልማት ማህበሩ እና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ አደራ ብለዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የጥቃት ጥበቃ ፖሊሲውን መተግበር ዜጎች በልማት ስራ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑንና ለተግባራዊነቱም የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡