በዳግም የትምህርት ዕድል ፕሮጀክት አተገባበር እና ዘላቂነት ዙሪያ ከባለድርሻ አካለት ጋር የምክከር መድረክ ተካሄደ፡፡

የወላይታ ልማት ማህበር ከሉሚኖስ ፈንድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በዳሞት ጋሌ፣ ቦሎሶ ሶሬ እና ባይራ ኮይሻ ወረዳዎች በሚተገብረው “Luminos Second Chance Education” ፕሮጀክት ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ በተለያየ ምክንያት በትምህርት ገበታ የማይገኙ ህጻናትን ወደ ትምህርት ቤት በመመለስ በአንድ ዓመት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል አስተምሮ ወደ 4ኛ ክፍል በማዛወር ከዕድሜ አቻዎቻቸው ጋር እኩል ያደርጋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዛሬው ዕለት በእስካሁን የፕሮጀክቱ አፈጻጻምና ዘላቂነት ዙሪያ ከወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ፣ ፕሮጀከቱ ከሚተገበርባቸው 3 ወረዳዎችና 9 ትምህርት ቤቶች ከተወጣጡ የትምህርት አመራሮችና አመቻቾች ጋር የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል፡፡ የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈተቱት የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ለፕሮጀክቱ አተገባበር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረው በመንግስት ደረጃም በፕሮጀክቱ የሚተገበረውን የተፋጠነ ትምህርት ፕሮግራም በወረዳዎቹ ለማላመድ እንሰራለን ብለዋል፡፡

የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ልማት ማህበሩ ፕሮጀክቱን ላለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ በማድረግ በርካታ ተማሪዎችን ተጠቃሚ እንደደረገ ጠቅሰው በመጪዎቹ ዓመታት በሌሎች አከባቢዎች በመተግበር ለማስፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

“Luminos Second Chance Education” ፕሮጀክት በወላይታ ዞን በሶስት ወረዳዎች እየተተገበረ ያለ ፕሮጀክት ሲሆን ለተማሪዎች ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ ወጪ በመሸፈን በአንድ ዓመት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል በማስተማር ወደ 4ኛ ክፍል በማዛወርና የተማሪዎችን ወላጆች ቁጠባ እንዲለማመዱ በማድረግ ወደፊት የቤተሰብ የገቢ አቅም ጎልብቶ ተማሪዎቹ በትምህርት ገበታ እንዲቆዩ ሁኔታዎችን የሚያመቻች ፕሮጀክት ነው፡፡