ወላይታ ልማት ማህበር ከጣሊያን መንግስት (Italian Presidency Council of Ministers) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የአርሶ አደሮችን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል የሚያስችል የግብርና ግብዓቶች ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩ ድጋፉን ያደረገዉ Farms for the Future ፕሮጀክት በኩል CEFA-ETS ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን በዞኑ ሁለት ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ነዉ።


ድጋፉ በኪንዶ ዲዳዬ እና በሁምቦ ወረዳዎች የሚገኙ 200 አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን ለእነዚህ አርሶ አደሮች የተለያየ የጓሮ አትክልት ዘር፣ በቆሎና ቦሎቄ ምርጥ ዘር እንዲሁም ዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያን ያካተተ ነዉ።
የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ድጋፉ አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን እንዲያሻሽሉ ያስችላቸዋል ፡፡
በወላይታ ልማት ማህበር በሚተገበረዉ Farms for the Future ፕሮጀክት አማካይነት ከዚህ በፊት ለአርሶ አደሮቹ ዘመናዊ የአስተራረስና አመራረት ዘዴ ላይ ስልጠና መሰጠቱ የሚታወስ ሲሆን በስልጠናዉ ዘመናዊ አስተራረስና የምርት ጥራት ማሻሻያ መንገዶች ላይ ትኩረት የተደረገባቸዉ ዘርፎች ናቸዉ።
ወላይታ ልማት ማህበር በወላይታ ዞን ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የግብርና ስራን ለማዘመን እና የአርሶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት ለማሻሻል ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነዉ።




