ወላይታ ልማት ማህበር ላለፉት 25 ዓመታት በሰራተኞች ቁርጠኝነትና በጠንካራ አመራር በህዝቡ ውስጥ ገብቶ በመስራት ሰፊና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን እያከናወነ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ እነዚህን ተግባራት ለማስፋፋትና ይበልጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ ቆይቶ የበላይ አመራር ለውጥ በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
በዛሬው ዕለት አዲስ የተመደቡ አመራሮች ከወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶች ሰራተኞች ጋር የስራ ትውውቅ አደርገዋል፡፡ በትውውቅ መድረኩ የተገኙት የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ ከትምህርት ቤቶቹ ሰራተኞች ጋር ከተዋወቁ በኋላ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶቸን በማጠናከርና በማስቀጠል ረገድ የሰራተኞቹ ሚና የጎላ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ማህበሩ ላለፉት ጊዜያት ጠንካራ ተቋማትን እየገነባ እንደቆየ ያነሱት ዶ/ር አበባየሁ እነዚህን ተቋማት ይበልጥ በማጠናከር የህዝቡን ተጠቃሚነት ከፍ ለማድረግ መስራት ከሁሉም የማህበሩ ሰራተኞች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል፡፡ አዲስ በቦዲቲ፣ አረካና ገሱባ ከተሞች ተከፍተው ስራ የጀመሩ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶች ከወላይታ ሶዶ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ጋር ተስተካክለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውና የሁሉም ትምህርት ቤቶች ደረጃ በተሻለ ሁኔታ አስፈላጊ ግብዓቶች ተሟልተው የልህቀት ማዕከልነታቸው እንዲቀጥል ማህበሩ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ልማት ማህበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ወንድሙ ወልዴ በበኩላቸው የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት የወላይታ ልማት ማህበር አምባሳደር በመሆኑ ማህበሩ በትኩረት ይመለከተዋል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማህበሩ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ተግባራት አንዱ የትምህርት ስራ ስለሆነ አሁንም ቢሆን በዚሁ ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ሰራተኞችም በትምህርት ቤቶቹ ለስራ አመቺ የሆነ ከባቢ በመፍጠርና ለውጤት የሚያበቃ አስራር በተሻለ ሁኔታ ተዘርግተው ለውጤት መሰራት እንዳለበት አስገንዝበው ከአዲሶቹ የስራ መሪዎች ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ወላይታ ልማት ማህበር በሰው ሀብት ልማት የትኩረት አቅጣጫ ዘርፍ ከሚተገብራቸው አበይት ተግባራት ውስጥ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን በትምህርት ቤቱ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ተማሪዎች ገብተው ራሳቸውን በአግባቡ በማብቃት ለቀጣይ የትምህርት ደረጃ በመዘጋጀት የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ ትምህርት ቤቱ ወጪ በመጋራትና በድጋፍ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ይታወቃል፡፡
Wolaytta Worqaa Mayzzana!








