ማህበሩ በዛሬው ዕለትም ከዚህ ቀደም አብሮት ከሚሰራው ET-LEARNS ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 310 ክሮም ኮምፒውተር እና 10 ሰርቨሮችን ከነአክሰሰሪያቸው ለተለያዩ ት/ቤቶች አበርክቷል ።
በመድረኩ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የወላይታ ልማት ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገብረመስቀል ጫላ የወላይታ ማህበረሰብ ያለውን ጥሪት ሀብቱን እንኳ ሳይሰስት ልጆቹን የሚያስተምር እና ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጥ መሆኑን በመግለፅ ት/ቤቶች ይህን የዛሬውን በማህበሩ የተበረከተውን ኮምፒውተር በሚገባ በመጠቀም ብቁ እና ተወዳዳሪ የሆነ ትውልድን የማፍራት ሀላፊነት እንዲወጡ በአፅንኦት አሳስበዋል።
ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑን በመረዳት በትምህርቱ ዘርፍ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት በማሰብ ይህን ድጋፍ ላበረከቱት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል ።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በንግግራቸው የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎቻችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በእውቀት በመደገፍ የውጤት ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ የማድረግ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ለሁለንተናዊ ለውጥ ትምህርት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም በየደረጃው በኃላፊነት ስሜት በመስራት ውጤት ለማምጣት መትጋት ይጠበቅበታል በማለት ይህን የተበረከተውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል እንዲሠራ አሳስበዋል ።
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ናና ማህበሩ በትምህርት ዘርፍ ለሚሰራቸው ሥራዎች መሳካት የግብረሰናይ ድርጅቶች፣ አባላቱ እና ደጋፊዎቹ ያላቸው ሚና የማይዘነጋ መሆኑን ገልፀዋል ።
ማህበሩ በዛሬው ዕለት “ET-LEARNS” ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመሆን በዞኑ ለሚገኙ አስር የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 310 ክሮም ኮምፒውተር እና 10 ሰርቨሮችን ማበርከቱን በመግለፅ ከዝህ ቀደምም ለ21 ትምህርት ቤቶች ያበረከተ ሲሆን በድምሩ ለ31 ትምህርት ቤቶች 992 ክሮም ኮምፒውተሮች እና 31 ሰርቨሮችን ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
አቶ ሱሌይማን ዳዊት የሳቫና ፕሪንትንግ ፕሬስ መሥራች እና ባለቤት የወላይታ ህዝብ የመማር እና የመለወጥ ፍላጎቱን መገንዘባችን ነው አብረን እንድንሰራ ያነሳሳን በማለት በቀጣይም አብሮነታቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል ።







