ወላይታ ልማት ማህበር ዜጎች የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማስቻል በያዘዉ ዕቅድ የተለያዩ ድጋፎችን በማመቻቸት የድርሻዉን እየተወጣ መቆየቱ ይታወቃል።
ማህበሩ ባሳለፍነዉ ዓመት በካዎ ኮይሻ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ዜጎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም ሂደት ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ የቆየ ሲሆን በዛሬዉ ዕለት በዞነነ አስተዳደርና በተለያዩ አካላት ድጋፍ የሰራቸዉን መኖሪያ ቤቶች በአደጋዉ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች አስረክቧል።
ቤቶቹን የሰራዉ በልማት ማህበሩ የሚተዳደረዉ አንጋፋው ዳሞታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር 120 ቤቶችን በተሰጠዉ የጊዜ ገደብ ሰርቶ በማጠናቀቅ ለተፈናቃዮች አስረክቧል።
በርክክቡ ስፍራ የተገኙት የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ናና ማህበሩ ባለፈዉ ዓመት አደጋዉ በተከሰተበት ወቅት ቃል በገባዉ መሰረት የአደጋዉ ሰለባዎችን በመደገፍና መልሶ በማቋቋም ስራ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። ለዚህም ማሳያዉ አደጋዉ በተከሰተበት ጊዜ ያደረገዉ የምግብ እህልና አልባሳት ድጋፍ እና አሁን ደግሞ ለተፈናቃዮቹ መኖሪያ ቤትን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በመስራት ማስረከቡ ነዉ ብለዋል።
በዛሬዉ ዕለት ተጠናቅቆ ርክክብ የተደረገዉ የተፈናቃዮች መኖሪያ ቤት፣4 ኪሎሜትር የዉሃ መስመር ዝርጋታ እና ቦኖ በአበላ አባያ ወረዳ ጮካሬ ቀበሌ በወላይታ ዞን አስተዳደርና ሌሎች አጋሮች ድጋፍ በወላይታ ልማት ማህበር ዳሞታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የተገነባ ነዉ።
ማህበሩ ተፈናቃዮችን በማቋቋም ሂደት ላበረከተዉ ጉልህ አስተዋጽኦ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ከወላይታ ዞን አስተዳደር ዕዉቅና ተሰጥቶታል።








