ወላይታ ልማት ማህበር የልማት ስራዎችን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ይሰራል። ማህበሩ በሰዉ ሀብት ልማት በአጋርነት ከሚሰራቸው ተቋማት አንዱ ሳቫና ፕሪንቲንግ ሲሆን ለዘንድሮ የትምህርት ዘመን በወላይታ ዞንና ወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል። ድጋፉ የደብተር፣ እስክሪብቶ እና ሞንቴሶሪ ዕቃዎችን ያካተተ እንዲሁም በገንዘብ ሲተመን ከ1.1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነዉ።
ማህበሩ ከዚህ በፊት ከዚህ ተቋም ጋር በመተባበር በወላይታ ዞን በሚገኙ በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ አቅመ ደካማ ተማሪዎች መሰል ድጋፍ እያደረገ ቆይቷል።
የዘንድሮ ድጋፍ የተደረገዉ በአረካ፣ ወላይታ ሶዶና ቦዲቲ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ዳሞት ጋሌ ወረዳ ሲሆን በነዚህ መዋቅሮች በሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች ላሉ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ነዉ።
ወላይታ ልማት ማህበር በየዓመቱ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በዞኑ ላሉ በርካታ አቅመ ደካማ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ይታወቃል።








