የወላይታ ልማት ማህበር ከSNV ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በBRIDGE+ ፕሮጀክት አማካይኝነት ከሚተገብራቸው ተግባራት መካከል አንዱ የትምህርት ቤቶች የወተት ምገባ ነው፡፡ በዚሁ ተግባር በቅድመ መደበኛ ያሉ ተማሪዎችን ንጽህናው የተጠበቀ አርጎ ወተት ከወላጆች ጋር በመነጋገር በመመገብ ህጻናቱ ጤንነታቸው እንዲሻሻል፣ የትምህርት አቀባበል ችሎታቸው እንዲዳብርና፣ የመጠነ መቅረትና ማቋረጥ ምጣኔ እንዲቀንስ እየሰራ ነው፡፡
በትላንትናው ዕለት (01/09/16 ዓ.ም) የወተት ምገባ ተግባር በሶዶ ከተማ አስተዳደር መርካቶ 1ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅድመ መደበኛ ክፍሎች በይፋ ተጀምሯል፡፡ ማህበሩ ባሳለፍነው ዓመት በዚህ ተግባር የተሳኩ ስራዎችን እንደሰራና በያዝነው የፈረንጆች በጀት ዓመትም በተመሳሳይ በሶዶ ከተማ በሚገኙ አስራ ሶስት ትምህርት ቤቶች የወተት ምገባ ስራ ለመስራት አቅዶ ወደ ተግባር መግባቱን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሌንጫ ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ባለፈው ዓመት በወተት ምገባ ከ2 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን በቀጣዮቹ 3 ዓመታት 25 ሺህ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ አስተባባሪው ጨምሮ ገልጸዋል፡፡
BRIDGE+ ፕሮጀክት ከSNV ኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና በትምህርት ቤቶች የወተት ምገባ ላይ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡