ወላይታ ልማት ማህበር በሰው ሀብት ልማት የትኩረት አቅጣጫ ዘርፍ የትምህርት መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ከመንግስት ጎን በመሆን ለትምህርት ተደራሽነትና ጥራት መረጋገጥ የራሱን ሚና ተወጥቷል፤ እየተወጣም ነው፡፡
ማህበሩ ከዚህ በፊት በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የመማሪያ ህንጻዎችን በመገንባት ለመንግስት ያስረከበ ሲሆን በዘሬው ዕለት በኦፋ ወረዳ ሙሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ብሎክ 8 የመማሪያ ክፍሎችን የያዘ ህንጻ ገንብቶ በማጠናቀቅ አስመርቆ ለወረዳው አስተዳደር አስረክቧል፡፡
ህንጻው የወላይታ ዞን አስተዳደር ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር ከ5.1 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እንደተገነባ የተናገሩት የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና የአካባቢው ማህበረሰብ ህንጻውን እንደራሱ ንብረት በአግባቡ ይዞ መንከባከብ እንዳለበት አደራ ብለዋል፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው አክለውም ልማት ማህበሩ ከዚህ በፊት በዚህ ወረዳ በተለያየ ቀበሌያት በርካታ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እንዳደረገ በማስታወስ በቀጣይም ከዞኑ አስተዳደርና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
በምረቃው ስነስርዓት የወላይታ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ መስፍን ቶማስ፣ የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚካኤል ሳኦል፣ የኦፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዴማ ኃይሌና ሌሎች የዞኑና የወረዳው የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡





