ወላይታ ልማት ማህበር በዘላቂነት የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በያዘው ዕቀድ በዞኑ ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና አስተራረስ እንዲለማመዱ ከተለያዩ ግብረሰናይ ደርጅቶች ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡ ማህበሩ የመስኖ እርሻንና የንብ ማነብ ስራን ለማዘመን፣ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ወዘተ… ስራዎችን በመስራት አያለ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንዳደረገና እያደረገ እንደቆየ ይታወቃል፡፡
ልማት ማህበሩ በዚሁ ዘርፍ በሚያደርገው ርብርብ GIZ የተሰኘ የጀርመን ግብረሰናይ ድርጅት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮና ከወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ጋር በትብብር ሰባት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የእርሻ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ ድጋፉ ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከማህበሩ ጋር በመተባበር በዞኑ ውስጥ የእርሻ ሜካናይዜሽን ለማሳደግ ባደረገው ስምምነት መሰረት መሆኑን የተናገሩት የማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ድርጅቱን ለድጋፉ በማህበሩ ስም አመስግነዋል፡፡ ድጋፉ የትራክተር ማረሻ፣ መከስከሻ፣ መስመር ማውጫና የኖራ መበተኛን ያካተተ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ድጋፉ የዞኑን አርሶ አደር ከተለምዷዊ አስተራረስ በማላቀቅ ከዘመናዊ አስተራረስ ጋር ለማለማመድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ያሉት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የልማት ማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ጴጥሮስ ወልደ ማርያም የዞኑ አስተዳደር በሚችለው ሁሉ ልማት ማህሩን መደገፍ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ጨምረውም የወላይታ ህዝብ ከልማት ማህበሩ ጎን በመቆም ማህበሩ ለሚያደርገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡





