ወላይታ ልማት ማህበር በሀገር አንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ስመጥር እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን በማፋራት የሚታወቀውን ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ለማጠናከርና ለማስፋፋት በያዘው ዕቅድ ባሳለፍነው ዓመት የሀብት ማሰባበሰቢያ መርሀ ግብር በመንደፍ የተለያዩ አካላትን በማሳተፍ ሀብት ማሰባበሰቡ ይተወቃል፡፡
ለትምህርት ቤቱ ማስፋፊያና ማጠናከሪያ ድጋፍ ለማድረግ በወቅቱ ቃል ከገቡ ባለሀብቶች መካከል ሀጂ ሙስጠፋ አወል (የሙለጌ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባለቤት) እና ቤተሰቡ አንዱ ናቸው፡፡ ባለሀብቱ ትምህርት ቤቱን ለመደገፍ አንድ ብሎክ የመማሪያ ክፍል ገንብተው ሙሉ የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት ለማስረከብ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ቃላቸውን በማክበር የህንጻ ስራውን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በማስጀመሪያው ስፍራ የተገኙት የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ባለሀብቱ ትምህርት ቤቱን ለመደገፍ የገቡትን ቃል ጠብቀው በዛሬው ዕለት ግንባታውን ስላስጀመሩ በወላይታ ህዝብና በልማት ማህበሩ ስም ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ አቶ አሰፋ ጨምረውም ይህ ግንባታው የተጀመረው ህንጻ የትምህርት ቤቱን የተማሪ ቅበላ አቅም ለማሳደግ እንደሚረዳ፣ ግንባታውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃና ሙሉ የውስጥ ቁሳቁስ በባለሀብቱ እንደሚሟላለት ተናግረዋል፡፡
በግንባታ ማስጀመሪያ ስፍራ የወላይታ ዞን እና ሶዶ ከተማ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች የተገኙ ሲሆን የመሰረት ድንጋዩን የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያም እና የሙለጌ ኃላ/የተ/የግ/ማህበር ባለቤት ሀጂ ሙስጠፋ አወል በጋራ በመሆን አኑረው ስራው በይፋ ተጀምሯል፡፡