ወላይታ ልማት ማህበር ከድህነትና ኋላቀርነት የተላቀቀ ወላይታን የማየት ትልሙን ለማሳካት በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የልማት ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ማህበሩ በ2024 እ.አ.አ በሰው ሀብት ልማት፣ በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያና በተቀናጀ ጤና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ በመነሳት ላለፉት 9 ወራት የልማት ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቶ አፈጻጸሙን ገምግሟል፡፡
በግምገማው ማህበሩ በዓመቱ በ9 ወራት ከ98 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ሀብት በመሰብሰብ የልማት ተግባራቱን በሁሉም የትኩረት አቅጣጫዎች በዕቅዱ መሰረት እንዳከናወነ ተገልጧል፡፡ ማህበሩ በዋናነት በሰው ሀብት ልማት ያከናወናቸው ተግባራት በጠንካራ ጎን የታዩ ናቸዉ፡፡ ለአብነትም በዓመቱ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ለማጠናከር መላው አባለቱንና ደጋፊዎቹን በማነቃነቅ አመርቂ ተግባራት መከናወናቸውንና በብሔራዊ እና ክልላዊ ፈተናዎች ተፎካካሪ በመሆን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ዝናውን አስጠብቆ መቆየት እንዲሁም ትምህርት ቤቱን በዞኑ ቦዲቲ፣ አረካና ገሱባ ከተማ አስተዳደሮች ስራ እንዲጀምሩ ማድረጉ ለልማት ማህበሩ ስኬት መሆኑ ተገምግሟል፡፡
ማህበሩ በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ያከናወነ ሲሆን በማህበር የተደራጁ ግለሰቦችን የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠና በመስጠትና ለስራ የሚያገልግሉ ቁሳቁሶችን በመስጠት፣ በወተት ማምረት ስራ የተሰማሩ የህብረት ስራ ማህበራትን በመደገፍና በማጠናከር፣ በሰርቶ ማሳያ ማዕከላት የግብርና ምርቶችን የማምረት.. ወዘተ ተግባራትን አከናውኗል፡፡
በተቀናጀ የጤና አገልግሎት ዘርፍ ደግሞ ለአካል ጉዳተኞችና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፎችን በማድረግ፣ የፈውስና ሪፌራል ህክምናዎችን በመስጠትና በማመቻቸት፣ ለአካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፎችን በማበርከት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡
በአጠቃላይ በዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት በጥልቀት የተገመገሙ ሲሆን በዚህም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ከ354 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡ በመጨረሻም በቀሪ ወራት የሚተገበሩ ተግባራትን ከዚህ በተሸለ ሁኔታ በመተግበር ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ታውቋል፡፡