ወላይታ ልማት ማህበር ከተቋቋመለት ዋንኛው ዓላማ አንዱ የበጎ አድራጎት ስራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከምስረታውም ጀምሮ በበጎ ስራ የሚታወቀው ይህ ማህበር መንግስት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ በዛሬው ዕለት በኪንዶ ኮይሻ እና ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳዎች ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ለቤት መስሪያ የሚሆን የቤት ኪዳን ቆርቆሮ እና ሚስማር ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን ለወረዳዎቹ አመራሮችና አቅመ ደካማ ቤተሰቦች በስፍራው በመገኘት ያበረከቱት የማህበሩ አባላት ልማትና ሀብት አሰባሰብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ባልጣ ማህበሩ ከአባላቱ ያሰባሰበውን ሀብት መልሶ ለማህበረሰብ ልማት እንደሚያውል ተናግረዋል፡፡ አቶ ዳንኤል ጨምረውም ማህበሩ እነዚህን ዓይነት አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ ዋናው ዓለማ አድርጎ እየሰራ እንደሆነ በማብራራት በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን አቅሙ በፈቀደ መጠን በራሱ አቅምና ከአጋሮች ጋር በመሆን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አውስተዋል፡፡
ማህበሩ ይሀንን ድጋፍ ለማድረግ እነዚህን ቤተሰቦች ወረዳዎቹ መልምለው ከሰጡ በኋላ እስከስፍራው በማቅናት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በማረጋገጥ በዛሬው ዕለት በሁለቱም ወረዳዎች ማለትም በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ ሞልትቾ እና በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ በሬዳ ቀበሌያት ለሁለት አቅመ ደካማ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 30 ቅጠል የቤት ኪዳን ቆርቆሮና 7 ፓኬት ሚስማር ነው፡፡ ድጋፉን የወረዳዎቹ አመራሮችና ድጋፍ የተደረገላቸው ግለሰቦች ልማት ማህበሩን በማመስገን ተረክበዋል፡፡