ለማህበሩ ፋይናንስ አመራሮችና ባለሙያዎች የፋይናንስ ሪፖርት ስልጠና ተሰጠ፡፡

የወላይታ ልማት ማህበር ከአባላቱ፣ ከረጂ ድርጅቶችና ከገቢ ማስገኛ ተቋማት የሰበሰበውን ሀብት ለታለመለት የልማት ግብ ለማዋል ሀብቱን በዘመናዊ የፋይናንስ አሰራር ይመራል፡፡ ማህበሩ መንግስታዊ ያልሆነና ለትርፍ ያልተቋቋመ የልማት ድርጅት እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን የፋይናንስ አሰራሮች ይከተላል፡፡ ይኼም የፋይናንስ አሰራር ስታንዳርድ IFRS/IPSAS (International Financial Reporting Standards/ International Public Sector Accounting Standards) ነው፡፡

ማህበሩ ለፋይናንስ አመራሮችና ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት የቆየ የፋይናንስ ሪፖርት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው የፋይናንስ ሪፖርት ስታንዳርዶች፣ የጥሬ ገንዘብ አስተዳደርና ንብረት ምዝገባ እና ሌሎች ሂሳብ ነክ ርዕሶች ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን ለፋይናንስ ሪፖርት ስራና ውስን የሆነውን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ በስልጠናው የመያድ (NGO) እና ቢዝነስ ተቋማት የሂሳብ አሰራሮችና ሪፖርት ስርዓት ተዳስሰዋል፡፡

የወላይታ ልማት ማህበር ለፋይናንስ አሰራር ዘመናዊ የሪፖርት ስታንዳርድ የሆነውን IFRS/IPSAS (International Financial Reporting Standards/ International Public Sector Accounting Standards) የሚጠቀም ሲሆን ይህም በሀገራችን የፋይናንስ አሰራር መሰረት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚገለገሉበት ነው፡፡

በ17 እና 18/09/16 ዓ.ም በተሰጠዉ ስልጠና የማህበሩ የፋይናንስና ኦዲት አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የግዥና ንብረት አፊሰሮች ሁሉም የገቢ ማስገኛ ተቋማት ሂሳብ ነክ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡