ለተፋጠነ ትምህርት መርሀ ግብር አመቻች መምህራን እና መርሀ ግብሩን ለተገበሩ ወረዳዎች ዕውቅና ተሰጣቸው፡፡
የወላይታ ልማት ማህበር በሰው ሀብት ልማት ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ Luminos Second Chance Education ፕሮጀክት ነው፡፡ ልማት ማህበሩ በዚሁ ፕሮጀክት በሶስት በባይራ ኮይሻ፣ ዳሞት ጋሌና ቦሎሶ ሶሬ ወረዳዎች ከሉሚኖስ ፈንድ ኢትዮጵያ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ እድሜያቸው ከ9-14 ያሉ ልጆችን ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ትምህርት ገበታ በማምጣት በተፋጠነ የትምህርት መርሀ ግብር በአንድ ዓመት ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል በማስተማር ወደ 4ኛ ክፍል በማዛወር ከዕድሜ አቻዎቻቸው ጋር እኩል ያደርጋል፡፡
ማህበሩ በትላንትናው ዕለት በቀን 04/11/16 ዓ.ም ለፕሮጀክቱ አመቻች መምህራንና ፕሮጀክቱን ከማህበሩ ጋር በጋራ ለተገበሩ ወረዳዎች የዕውቅና መርሀ ግብር በማዘጋጀት ሽልማት፣ ሜዳሊያ እና ዋንጫ አበርክቶላቿል፡፡
በዓመቱ በፕሮጀክቱ ስራ የተሸለ አፈጻጸም ያሳዩ አመቻች መምህራን ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ለወረደዎችም የሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማት ተሰጥቷቿል፡፡ ከወረዳዎች የባይራ ኮይሻ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት የተፋጠነ መርሀ ግብርን በመተግበርና በአጠቃላይ አፈጻጸም የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በመርሀ ግብሩ የልማት ማህበሩ የኢንተርፕርነርሺፕና ገቢ ማስገኛ ተቋማት ማስተባበሪያ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ፈለቀ ለፕሮጀክቱ መሳካት የድርሻቸውን ላበረከቱ ሁሉም አካላት ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን መምህራን ስራዎቻቸውን ሲከውኑ ለሙያቸው በመሰጠት በእውቀትና አመለካከት የተሻለ ተተኪ ትውልድን ማፋራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
Luminos Second Chance Education ፕሮጀክት ወላይታ ልማት ማህበር ላለፉት አራት ዓመታት ከሉሚኖስ ፈንድ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በወላይታ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ከ2,350 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው፡፡