የኩባንያው የግንባታ ስራዎች አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የዳሞታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለወላይታ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገንብቶ ያጠናቀቀውን ቢሮ ባስረከበበት ወቅት ነው፡፡
በወላይታ ልማት ማህበር የሚተዳደረው የዳሞታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ጥራት ያላቸውን ግንባታዎች በከፍተኛ ጥራትና ፍጥነት ገንብቶ እንደሚያጠናቅቅ ይታወቃል፡፡ ኩባንያው ከግንባታ ስራዎች በተጨማሪ ማሽኔሪዎችን በማከራየትና ሲሚንቶ በማከፋፈል ለህብረተሰቡ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ኩባንያው በዛሬው ዕለት ለወላይታ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገንብቶ ያጠናቀቀውን የቢሮ ህንጻ የወላይታ ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት አስረክቧል፡፡ በርክብክቡ ስነስርዓት የተገኙት የወላይታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ እና አቶ ዘውዱ ሳሙኤል የኩባንያው የግንባታዎች አፈጻጸም አቅም በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በመናገር ይህ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የመምሪያውን ህንጻ በዞኑ በተለያዩ ሴክተሮች ያለውን የቢሮ ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና በበኩላቸው ከማህበሩ የገቢ ማስገኛ ተቋማት አንዱ የሆነው ዳሞታ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የሚሰራቸውን የግንባታ ስራዎች በፍጥነትና በከፍተኛ ጥራት እያከናወነ እንደሆነ ገልጸው የዞኑ አስተዳደር ሂደቱን በመከታተል በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ላደረገው ትብብር አመስግነዋል፡፡
የወላይታ ዞን ሰራተኛና ማህራዊ ጉዳይ መመሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ኩማ ይህ አዲሱ ህንጻ ከዚህ በፊት በመምሪያው የነበረውን የቢሮ ጥበትና ምቹ ያልሆነ የስራ አካባቢ ችግርን እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡