ማህበሩ በወላይታ ሶዶ ከተማ ከሚገኙ የፌዴራልና ክልል ተቋማት እንዲሁም የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጋር በልማት ዙሪያ ዉይይት አካሄደ።
በዉይይት መድረኩ ልማት ማህበሩ የአባላትን ቁጥር በማሳደግና የገቢ ማስገኛ ተቋማትን በማጠናከር ከለጋሾች ድጋፍ በመላቀቅ በራሱ እግር መቆም እንዳለበት በአጽንኦት አስተያየት ተሰጥቷል። በተጨማሪም የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑ ተመልክቷል።
ዉይይቱን የማህበሩ የበላይ ጠባቂና የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ እና የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ናና በጋራ በመሆን የመሩት ሲሆን ዋና አስተዳዳሪዉ በከተማዉ የሚገኙ ተቋማት ለማህበሩ የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ልማት ድንበር የሌለዉ በመሆኑ ሁሉም አካላት በማህበሩ ጎን እንዲቆሙ አደራ ብለዋል።
በዉይይት መድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ረዳት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ አቶ ዮሐንስ በየነ፣ የወላይታ ዞን አስተዳደር የስራ አስፈፃሚ አባላት፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኙ የፌዴራልና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የግል ባንኮች እና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኃላፊዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።




