የወላይታ ልማት ማህበር ከተለያዩ ሀገር በቀልና አለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የልማት ተግባራትን ያከናውናል፡፡ ማህበሩ በትኩረት ይዞ ከሚሰራቸው የልማት ተግባራት አንዱ በሆነው የተቀናጀ ጤና በመሰረተ ማህረሰብ ተሃድሶ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አካል ጉዳተኞችን ያካተተ የልማት ተግባራትን እያከናወነ ቆይቷል፤ እያከናወነም ነው፡፡
ማህበሩ በዛሬው ዕለት ከአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ጋር በትብብር መስራት የሚያስችል ስምምነት አድርጓል፡፡ ልማት ማህበሩና ተሃድሶ ማዕከሉ የሚተገብሯቸውን ለአካል ጉዳተኞች የሚደረጉ የተሃድሶ አገልግሎቶችን በጋራ ለመተግበር ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በዚህም መሰረት የተሃድሶ አገልግሎቶችን ለአካል ጉዳተኞች ሁለቱ ተቋማት በጋራ የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡
ስምምነቱ የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና እና የአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኢዮብ እንዳለ በወላይታ ልማት ማህበር ዋና ጽ/ቤት በተገኙበት ተደርጓል፡፡
የአርባምንጭ ተሃድሶ ማዕከል ከዚህም በፊት በተለያየ ጊዜ ከማህበሩ ጋር በመተባበር ለአካል ጉዳተኞች የተሃድሶ አገልግሎት እየሰጠ የቆየና ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ልማት አስተባበሪነት በወላይታ ዞን በጉኑኖ ሐሙስ፣ በዴሳ እና ቦዲቲ ከተሞች ለ200 አካል ጉዳተኞች የአካል ድጋፍና ሪፌራል ህክምና አገልግሎት እንደሰጠ ይታወሳል፡፡