የጉባኤውን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ እና የወላይታ ልማት ማህበር ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደተናገሩት ወላይታ ማንነቱን ጠብቆ የኖረ፤ የዳበረና ተዝቆ የማያልቅ ባህል ያለው ህዝብ ነው። የወላይታ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ፣ በመቻቻልና በመከባበር ከሌላው ጋር አብሮ የሚኖር ድንቅ እሴቶች ባለቤት ነው። የዘመኑ ትውልድ የአባቶችን ጠንካራ የሥራ ባህልን፣ ጀግንነትን፣ አብሮነትን እና መከባበርን መርህ በማድረግ ለወላይታ ልማት መትጋት ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል።

የህዝባችንን ድንቅ እሴቶች በመጠቀም ዛሬ በቴክኖሎጂ በግብርና ሜካናይዜሽን እና በሥራ ባህል በመለወጥ ለማደግ መትጋት አለበት ብለዋል። ህዝባችንን ከድህነት እንዲወጣ ማህበሩ የያዘውን ወላይታ በልጽጎ የማየት ራዕይ እውን እንዲሆን በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ እንደተናገሩት ወላይታ ልማት ማህበር ለወላይታ ህዝብ ልማት ብሎም ለሀገራችን ብልጽግና ዕውን መሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
በለውጡ መንግሥት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ እንዲያሳኩ ምቹ ፖሊሲ በማዘጋጀት የተጣለባቸውን እንዲወጡ መደረጉን አንስተው ልማት ማህበሩ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት እንዲመጣ እየተጋ ይገኛል ብለዋል። የያዘውን ዓላማ ከግቡ ለማድረስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት አጋርነት እና ርብርብ ይጠይቃል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የዞኑ መንግሥት የፋይናንስ፣ የሀሳብ እና ሌሎችንም ድጋፎች እያደረገ ይገኛል ብለዋል። ማህበሩን በዘላቂነት ለማጠናከር ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

ዋና አስተዳዳሪው በፍጥነት እያደረገ የመጣውን የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ብዙ ሥራ ይጠይቃል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አበባየሁ ቶራ እንደተናገሩት ልማት ማህበሩ ከአባላቱ፣ ከደጋፊዎች፣ ከህዝቡ ከመንግሥት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት በሚገኝ ድጋፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ልማት ማህበሩ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ልማት በሰው ሀብት ልማት ውጤታማ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ መሆኑን በመጠቆም በመንግሥት የማይሸፈኑ የልማት ፍላጎቶችን እያሟላ እንደሚገኝ አብራርተዋል። ማህበሩ የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት እንዲያስችል የአደረጃጀትና የአሠራር ማሻሻያ በማድረግ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ እና በጥራትና በፍጥነት ለማሻሻል አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየተጋ ይገኛል ብለዋል።

ማህበሩ በዞኑ መንግሥት ድጋፍ ወደ ቀደመው ገናናነት እንዲመለስ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው የግብርና ሜካናይዜሽን በማረጋገጥ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል። ለማህበሩ ውጤታማነት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጉባኤው ጠቃሚ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ጠቅላላ ጉባኤዉ የተለያዩ ዉሳኔዎችን በማሳለፍና አስተዋጸኦ ላበረከቱ አካላት ዕዉቅና በመስጠት ተጠናቀቀ።
የወላይታ ልማት ማህበር 25ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬዉ ዕለት በወላይታ ጉታራ በድምቀት ተካሂዷል። በጉባኤዉ ከፌዴራል ጀምሮ በተለያየ መዋቅሮች የሚገኙ የወላይታ ተወላጆችና የልማት ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተሳትፈዋል።

በጉባኤው የ2025 እ.አ.አ የስራ አፈጻጸም ረፖርትና የ2026 ዕቅድ በልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በዶ/ር አበባየሁ ቶራ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎና አስተያየት ተሰጥቶ ጸድቀዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ከጉባኤ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንዲሁም የበጀትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርት በኮሚቴዉ ሰብሳቢ በክብርት ወ/ሮ እመቤት ወንድሙ ቀርቦ ጸድቋል። በመጨረሻም ልማት ማህበሩ በዓመቱ ላስመዘገባቸዉ ስኬቶች የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትና ተቋማት ሽልማትና የዕዉቅና ምስክር ወረቀት ተበርክቶ ተጠናቅቋል።


