ወላይታ ልማት ማህበር ላለፉት 16 ዓመታት በዞኑ ማዕከል ወላይታ ሶዶ አንድ ትምህርት ቤት ከፍቶ ብሩህ አዕምሮ እያላቸው በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት ጥራት ያለውን ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን ሙሉ ስኮላርሺፕ በመስጠትና ወጪ የሚጋሩ ተማሪዎችን በመቀበል ጥራት ያለውን ትምህርት በመስጠት ከወላይታ ዞን አልፎ በደቡብ ክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የህክምና ዶክተሮችን፣ መሀንዲሶችንና በሌሎች ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን አፍርቷል፤ እያፈራም ይገኛል፡፡
ማህበሩ በ2017 ዓ.ም የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት አድማስን በማስፋት በዞኑ ሶስት ማዕከላት ሶስት ትምህርት ቤቶችን በመክፈት ለህብረተሰቡ ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽነት ለማስፋት እየሰራ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የተከፈቱት በአረካ፣ ቦዲቲ እና ገሱባ ከተማ አስተዳደሮች የአካባቢዎቹንም ወረዳዎች ወረዳዎች እንዲያገለግሉ በማማከል ነው፡፡
እነዚህ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የተከፈቱ የወላይታ ሊቃ አረካ፣ ቦዲቲ እና ገሱባ ትምህርት ቤቶች በአሁን ሰዓት የመማሪያ ክፍሎችንና አስተዳደር ህንጻዎች በማዘጋጀት የተማሪዎችን ምዝገባ በማከናወን፣ የመግቢያ ፈተና በመፈተንና ሌሎች ለትምህርት ስራ አስፈላጊ ነገሮችን በማሟላት ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን ከ7ኛ ክፍል የሚጀምሩ ሲሆን በቀጣይ ከ8ኛ ክፍል ጀምሮ ያሉትን የሚቀጥሉ ይሆናል፡፡ የእነዚህ ትምህርት ቤቶች መከፈት ልማት ማህበሩ የሚያስተዳድራቸውን ትምህርት ቤቶች ቁጥር ወደ አራት ከፍ ያደርጋል፡፡