ልማት ማህበሩ በወላይታ የሚተገብራቸዉን የልማት ተግባራት ለማከናወን የልዩ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሀግብር አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከማሰባሰቢያ ስልቶች ዋና ዋና የሆኑት የአጭር መልዕክት ቁጥርና ቴሌብር አካዉንት ይገኛሉ።
ማህበሩ በዛሬዉ ዕለት እነዚህን የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን በይፋ አስተዋዉቋል። የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራ አጭር መልዕክት ቁጥሩንና ቴሌብር አካዉንት አጠቃቀሙን አስተዋዉቀዉ በአማራጮቹ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማህበሩን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረ/ፕ/ር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸዉ ሁሉም የማህበሩ አባላት በአጭር መልዕክት ቁጥርና ቴሌብር አማራጮች ለማህበሩ የሚደረገዉን ድጋፍ በማጠናከርና እርስ በርስ በመደጋገፍ ማህበሩ የጀመራቸዉን የልማት ተግባራትን ከዳር ማድረስ አለብን ብለዋል። አገልግሎቶቹንም በይፋ አስጀምረዋል።



የወላይታ ልማት ማህበር የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የደቡብ ኢትዮጵያ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ወላይታ ልማት ማህበር ከምስረታዉ ጀምሮ በርካታ የህብረተሰቡን ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን እንዳከናወነ ገልጸዉ እነዚህን ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁላችን ድጋፍ ያሻዋል ብለዋል።
የማህበሩ ስራ አመራር ቦርድ ማህበሩን ለማጠናከር ያደረገዉ ሪፎርም ማህበሩ እንዲጠናከር አድርጓል ብለዋል።
ልማት ማህበሩ በዛሬዉ ዕለት ያስተዋወቀዉ የአጭር መልዕክት ቁጥር 6368 ሲሆን በተጨማሪ የቴሌብር አካዉንትም በይፋ ወደ አገልግሎት ገብቷል። በሁለቱ አማራጮች 25 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።





