ወላይታ ልማት ማህበር በሰው ሀብት ልማት ዘርፍ ከአጋር ድግርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ ከነዚህ አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከመንግስት ጎን በመሆን የራሱን ድርሻ አበርክቷል፤ እያበረከተም ነው፡፡
ማህበሩ በዛሬው ዕለት በወላይታ ዞን አምስት መዋቅሮች የሚተገብረውን የዳግም ትምህርት ዕድል ፕሮጀክት አስጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልልና ከወላይታ ዞን ከተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተገኙ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወላይታ ጉታራ ሆቴል፣ ቱሪዝምና ስልጠና ማዕከል በይፋ መጀመሩን የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የአንድ ዓመት ቆይታ እንዳለውና በዞኑ ዳሞት ጋሌ፣ ቦሎሶ ሶሬና ባይራ ኮይሻ ወረዳዎች እና ቦዲቲና አረካ ከተማ አስተዳደሮች ከብር 15 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ የሚተገበር መሆኑንም አቶ አሰፋ ጨምረው ተናግረው በያዝነው በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ከነበረው በተለየ መልኩ ከመንግስት ጋር የሚሰራው የተፋጠነ ትምህርት መርሀ ግብር ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ተገኙ ባለድርሻ አካላትም ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነትና ስኬት የበከኩላቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ቃል ገብተው ማህበሩ ከዚህ በፊት በፕሮጀክቱ ባለው መልካም አፈጻጸም ተሞክሮውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
ይህ በዛሬው ዕለት የተጀመረው የዳግም ትምህርት ዕድል ፕሮጀክት ማህበሩ ከሉሚኖስ ፈንድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን ዕድሜያቸው ለትምህርት ደርሶ በተለያዩ ምንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ልጆችን በተፋጠነ የትምህርት መርሀ ግብር ከዕድሜ አቻዎቻቸው ጋር እኩል ማድረግ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃለፊ አቶ ሚካኤል ሳኦልን ጨምሮ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከወላይታ ዞን እንዲሁም ፕሮጀክቱ ከሚተገበርባቸው መዋቅሮች የተወከሉ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡








