ወላይታ ልማት ማህበር አሜሪካን ሀገር ኮሎራዶ ግዛት ዴንቨር ከተማና አካባቢው ከሚገኙ የወላይታ ተወላጆች ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ወላይታ ሶዶ ከተማ በመምጣት ኑሮአቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ህጻናትን ወደቤተሰቦቻቸው በመመለስ ማቋቋሙ ይታወቃል፡፡
ማህበሩ እነዚህን ህጻናት በማቋቋምና በዘላቂነት የልጆቹን ቤተሰብ ኑሮ ለማሻሻል በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ የሚታወስ ሲሆን ለልጆቹ የትምርት ቁሳቁስ፣ ቀለብ፣ የጤና መድህን ሽፋንና ሌሎች ድጋፎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ማህበሩ በዛሬው ዕለት ለልጆቹ ቤተሰቦች በዘላቂነት ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉና በንግድ ስራ ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ የመነሻ ካፒታል አበርክቷል፡፡ በዛሬው ዕለት በሶዶ ከተማ ለሚገኙና በእንጀራ መጋገር ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ለ9 ልጆች ቤተሰቦች 2 መቶ ሺህ ብር የሚያወጣ ጤፍ፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ከነምጣድ፣ ባለ 100 ሊትር ማቡኪያ ዕቃና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ተበርክተዋል፡፡ የወላይታ ልማት ማህበር ኢንተርፕርነርሺፕና ገቢ ማስገኛ ተቋማት ማስተባበሪያ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ፈለቀ በስፍራው ተገኝተው ለልጆች ወላጆች ጠንከረው ሰርተው ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት እንዲላቀቁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በቀጣይ ጊዜ ለተቀሩ ልጆች ወላጆች በሌሎች የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ ሁኔታዎችን እያመቻቸ መሆኑን ደግሞ በማህበሩ የእቅድ ዝግጅትና ፕሮግራም ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ሌንጫ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ወላጆች በጥራጥሬ ንግድና መሰል ጥቃቅን ንግድ ላይ ሰርተው ራሰቸውን እንዲችሉ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ወላየይታ ልማት ማህበር በ2023 እ.አ.አ ኑሮአቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ 28 ህጻናትን መልሶ ወደ ቤተሰብ በመቀላቀል በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ማድረጉ ይታወሳል፡፡







