ወላይታ ልማት ማህበር በዞኑ በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘመናዊ አሰራሮችን በመተግበር የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ይሰራል፡፡
ማህበሩ ባሳለፍነው ዓመት ከወላይታ ዞን አስተዳደርና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ይህንን የቴክኖሎጂ ሽግግር ስራን ለማሳደግ የስራ መሪዎች በሀገረ አየርላንድ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ወቅት የስራ መሪዎቹ የተለያዩ ኩባንያዎችን የጎበኙ ሲሆን የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ተጠቃሽ ነው፡፡
በወቅቱ በተደረገው ጉብኝት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና ከልማት ማህበሩ ጋር ለመስራተ ከተስማማው የትራክተር ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት የሆኑት ሚስተር ሮጀርስ ከልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጸሚ ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይታቸውም ከልማት ማህበሩ ጋር በትብብር በግብርና ሜካናይዜሽን ስራ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለቸውና በዚህም የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ ከማህበሩ ጋር በመሆን የትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ በመስራትና የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ለመስራት ፍላጎት እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አበባየሁ ቶራም ማህበሩ ከዚሁ ኩባንያ ጋር ለመስራት ደስተኛ እንደሆነ ተናግረው ስራው ልማት ማህበሩ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ ዶ/ር አበባየሁ ከውይይቱ በኋላ የልማት ማህበሩን አውቶሞቲቭ ጋራዥና የቢሮና ቤት ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት ያላቸውንና ከኩባንያው ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን መሰረተ ልማቶች አስጎብኝተዋል፡፡
በውይይቱ የወላይታ ልማት ማህበር ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ወንድሙ ወልዴና ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ብርሃኑ ኩማ ተሳትፈዋል፡፡
Wolaytta Worqaa Mayzzana!







