Dec 17, 2020
የወላይታ ልማት ማህበር በዞኑ ውስጥ ያለውን ስራ አጥነትና ድህነትን ለመቀነስ ብሎም ከድህነት የተላቀቀ ወላይታን የማየት ራዕዩን ለማሳካት ከ2018 እ.አ.አ. ጀምሮ ግዙፍና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልጉ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በአካባቢው የኢንዱስትሪ አብዮት እንዲቀጣጠል መሰረት ጥሏል፡፡ ለፕሮጀክቶቹ የሚያስፈልግ ሀብት ለማሰባሰብ ባደረገው ጥረትና የዞኑ መንግስት ባደረገው ከፍተኛ እገዛ ፕሮጀክቶችን እውን እያደረገ አንዳንዶችን እያጠናቀቀ የሚገኝ ሲሆን አንዳነዶቹን ጀምሯል፡፡
ልማት ማህበሩ ከሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሶዶ ከተማ የሚገነባ ዘመናዊ የተሸከሪካሪ ጥገና ጋራዥ ነው፡፡ ጋራዡ በሶዶ ከተማ ገንደባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገነባና የግንባታ ስራው ተጀምሮ የወለል ስራ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን የግድግዳ ስራውም ተጀምሯል፡፡ ከ4.9 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነባው ይህ ጋራዥ ሲጠናቀቅ በወላይታ ዞንና በአካባቢው ያለውን የጥገና ጋራዥ ችግርን በመቅረፍ ለተሸከሪካሪ ጥገና የሚወጣውን ከፍተኛ የገንዘብና ጉልበት ወጪ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም የዕውቀት ሽግግር ይፈጥራል፤ ለአካባቢው ዜጎች በመስኩ የስራ ዕድልም ይፈጥራል፡፡
ጋራዡ የሚገነባው የዞኑ መንግስት ለልማት ማህበሩ ባደረገው የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ግንባታውን ደግሞ በዞናችን በተለያዩ አካባቢዎች ግንባታዎችን በጥራትና በፍጥነት በማከናወን የሚታወቀው የዳሞታ ኮነንስትራክሽን ኩባንያ መሆኑን ከማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ክፍል የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡