የወላይታ ልማት ማህበር ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በአkባቢው ልማት በመሰማራት በዞኑ በጎ ለውጦችን በማስመዝገብ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ ትኩረት አድርጎ በሚንቀሳቀስባቸው በሰው ሀብት ልማት፣ በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ እና በተቀናጀ ጤና አጋር ድርጅቶች በትብብር የሚሰሩ ሲሆን በዚህም ከበርካታ ተቋማት ጋር በመስራት የካበተ ልምድ አለው፡፡
ማህbሩ በዛሬው ዕለት “Building Resilience through Education (BRTE2)” ከተሰኘ ፕሮጀክት ጋር በወላይታ ዞን የግብርና ትምህርትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋም በሚያደርገው እንቅስቃሴ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር ወርክሾፕ አከሂዷል፡፡ በምክክር መድረኩ የተገኙ ከወላይታ ዞን ከተለያዩ ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ አካላት በዞኑ ያለው እምቅ የግብርና አሰራርና ልምድ ለመቋቋም ለታሰበው የወላይታ ግብርና ትምህርትና ምርምር ማዕከል አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በምክክር ወርክሶሾፑ የተገኙት የወላይታ ዞን አስተዳዳር ጽ/ቤት ኃላፊና የዋና አስተዳዳሪው ተወካይ አቶ ፃድቁ ፈለቀ በትብብር በመስራት የግብርና ስራችንን ማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ በፊት የወላይታ አከባቢ የሚታወቅበትን የቆየ ዘመናዊ የግብርና አሰራርን እንደገና በማላመድ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና የወላይታ አከባቢ ከዚህ በፊት በዋዱ (WADU- Wolaita Agricultural Developmenet Unit) ለሀገራችን የግብርና ዕድገት ምሳሌ የነበረ በመሆኑ አሁንም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በመስራት መድገም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
በምክክር መድረኩ “Building Resilience through Education (BRTE2)” ፕሮጀክት ተወካዮችና በወላይታ ዞን የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

