ይህ የወተት ምገባው ፕሮግራም በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር እና በወላይታ ልማት ማህበር SNV BRIDGE+ ፕሮጀክት ትብብር በከተማው ባሉ 8 የመንግስት ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች ላይ እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን አጠናክሮ ለማስቀጠል በማሰብ ከማህበሩ ማኔጅመንት አባላት እና ከተወጣጡ ከማህበሩ ሠራተኞች ጋር ውይይት ተደርጓል ።
በመድረኩ የተገኙት የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ናና በንግግራቸው ማህበሩ ይህን ፕሮግራም አስጀምሮ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ እየተገበረ መቆየቱን በማስታወስ ቀጣይነቱ ላይ ግን ከፕሮጀክት ባለፈ ይበልጥ መታሰብ ስላለበት ነው ይህ ውይይት ያስፈለገው ብለዋል።
ጤናማ ትውልድን መገንባት ለሀገር እድገት መሰረት የሆነ ተግባር መሆኑን ጠቁመው አጋር የሆኑ አካላትንም በማመስገን ሁሉም ተሳታፊ አንድ ህፃንን ከወተት ለይቶ ማሰብ እንደማይቻል በመገንዘብ ሀላፊነት ተቀብሎ መነሳት እንዳለበትም አሳስበዋል ።
በመድረኩ ተገኝተው ከማህበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጋር ዉይይቱን የመሩት የሶዶ ከተማ ከንቲባ አማካሪ እና የከንቲባ ተወካይ አቶ ፍሰሀ ፀጋዬ በዚህ የትምህርት ቤት የተማሪዎች ወተት ምገባ ፕሮግራም ላይ ሰፊ ሥራ እንደሚጠበቅ በመግለፅ በከተማ አስተዳደር በኩልም ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በጀት ተመድቦለት ከፕሮጀክቱ ጋር በጋራ በከተማው በስምንት ቅድመ መደበኛ ት/ቤቶች ላይ እየተሰራ ያለ እና በቀጣይ በ23 ት/ቤቶች 6500 ህፃናትን ለመመገብ ታቅዶ እየተሰራ ያለ ቢሆንም በሶዶ ከተማ ካሉ ት/ቤቶች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ግን እጂግ ዝቅተኛ መሆኑንም ገልፀዋል ።
በመሆኑም ሥራውን ለማስቀጠል ይህ ቢቻውን በቂ ስላይደለ ሁላችንም ሀላፊነት በመውሰድ ከልጆቻችን እኩል ተማሪዎችን ለመመገብ ብንችል በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል ።
በወላይታ ልማት ማህበር የSNV- BRIDGE+ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሌንጫ በበኩላቸው ይህ ፕሮግራም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በትኩረት እንዲከታተሉ ከማድረግ ባሻገር መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ እያደረገ ያለ መርሃ ግብር መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ፕሮጀክት ማለት የሁልጊዜ ቆይታ ያለው ባለመሆኑ ፕሮግራሙ ተጀምሮ እንዳይቋረጥ በልጆቹ ላይ የተስተዋለው ለውጥ እና ፈገግታቸውም እንዲቀጥል ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ መሰራት እንዳለበትም ጠቁመዋል ።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማስቀጠል እንደሚተጉ ቃል በመግባት አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ማለትም አንደም ይሁን ሁለት ተማሪዎችን አቅማቸው በፈቀደው ልክ ለመመገብ እና በአቅራቢያቸው ያሉትን በማስተባበር ለቀጣይነቱ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል ።








