የወላይታ ልማት ማህበር ከባድ ማሽነሪዎችና መሳሪያዎች አስተዳደርና ኪራይ ድርጅት የስራ አድማሱን በማስፋት የትራክተር ኪራይን ወደ ሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ለማዳረስ እየሰራ ነው፡፡
ተቋሙ በአሁን ሰዓት በወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር፣ በሶዶ ዙሪያና ኦፋ ወረዳዎች የትራክተር ኪራይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ይህ ከታች ያለው ፎቶ በኦፋ ወረዳ አስተዳደር ማንቻ ቀበሌ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ ያሳያል፡፡

ወላይታ ልማት ማህበር በተመጣጣኝ ዋጋ ባቀረበዉ ትራክተር ተጠቃሚ መሆናቸውን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የቡጌ ዋንቼ አርሶ አደሮች አስታወቁ።

በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የቡጌ ዋንቼ ቀበሌ አርሶ አደር ታደሰ ታንጋ እና አብረሃም ማርቆስ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው በበሬ ሲታረስ የጉልበት የገንዘብ እና የጊዜ ብክነት እንደነበር ገልጸዋል። ለእርሻ ስራ የሚውል በሬ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በመጠየቁ ለግብርና ስራቸው ማነቆ መሆኑን ተናግረው የወላይታ ልማት ማህበር እና የሶዶ ዙሪያ ወረዳ አስተዳደር በጋራ በመቀናጀት በተመጣጣኝ ዋጋ ባቀረቡት ትራክተር መጠቀም መቻላቸውን ተናግረዋል ። አርሶ አደሮቹ ትራክተሩ የገንዘብ ወጪ ብቻ ሳይሆን የጉልበት እና የጊዜ አጠቃቀምን እንደቀነሰላቸውም አብራርተዋል። የወላይታ ልማት ማህበር የከባድ መሳሪያዎች ኪራይና አስተዳደር ስራሲኪያጅ አቶ ዘለቀ ባልቻ በበኩላቸው ልማት ማህበሩ ለወላይታ አካባቢ ህብረተሰብ በትምህርት በግብርና በጤና መንግስት በማይደርስባቸው የልማት ስራ ከመንግስት ጎን በመሆን በርካታ የልማት ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚታወቅ ማህበር ነው። ልማት ማህበሩ የወላይታ አካባቢ አርሶ አደሮችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገንዘብ ጊዜ እና ጉልበት ለመቆጠብ ያስችል ዘንድ 20 ትራክተሮችን በማስገባት 1ሄክታር መሬት በብር 10 ሺህ በማከራየት በርካታ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል። የሶዶ ዙሪያ ወረዳ ብልጽግና ፓሪቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ወንድሙ ታከለ እንዳሉት ልማት ማህበሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ እያደረገ ያለው አስተዋዕጾ የሚበረታታ ነው። የሶዶ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ከወላይታ ልማት ማህበር ጋር በመቀናጀት ከ7000 በላይ አርሶ አደር ማሳ በትራክተር በማረስ ወጪያቸውን ጉልበታቸውንና ጊዚያቸውን ለመቀነስ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።