ወላይታ ልማት ማህበር ሀገር በቀል፣ ለትርፍ ያልቆመ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን የተመሰረተው በ1950ዎቹ ቢሆንም በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ የገባው በ1993 ዓ.ም ነው፡፡ ማህበሩ በተሻሻለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 መሰረት ተመዝግቦ ህጋዊ ፈቃድ በማግኘት ለህዝብ ተጠቃሚነት እየሰራ ይገኛል፡፡ የማህበሩ ዋና ጽ/ቤት በዞኑ ዋና ከተማ ሶዶ ሆኖ በዞኑ ውስጥ ባሉ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች፤ ከዞኑ ውጭ ደግሞ በስምንት ከተሞች በአዲስ አበባ፣ አሚባራ፣ አርባምንጭ፣ ዲላ፣ ሐዋሳ፣ ሐዳሮ፣ መተሃራ እና ሻሸመኔ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን በመክፈት አገልግሎት አየሰጠ ይገኛል፡፡
ልማት ማህበሩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የወላይታን ዞን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ከመንግስት ጎን በመሆን የራሱን አዎንታዊ ሚና ሲጫወት ቆይቷል፡፡
ልማት ማህበሩ ከድህነትና ኋላ ቀርነት የተላቀቀች ወላይታን የማየት ራዕዩን ለማሳካት ከአባላት በሚገኝ የገንዘብ መዋጮ፣ ከአጋር ድርጅቶች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍና በስሩ ከሚገኙ ተቋማት በሚያገኘው ገቢ በሰው ሀብት ልማት፣ በተቀናጀ ጤናና ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ የትኩረት አቅጣጫዎች የዞኑን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ የልማት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ልማት ማህበሩ ለአካባቢውና ሀገራዊ ዕድገት የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት ሁሉም አባላት እስካሁን በእውቀታቸውና በገንዘባቸው ውድ ጊዜያቸውን ሰውተው የየራሳቸውን ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩትን አስተዋጽኦ እንዲቀጥሉ፤ አጋሮቻችን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ ሁሌም ከማህበሩ ጎን ለቆሙ አባላት፣ አጋር ድርጅቶችና ደጋፊዎቻችን በሙሉ ያለኝን ልባዊ ምስጋናና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡