የወላይታ ልማት ማህበር ላለፉት ጊዜያት በወላይታ ዞን በቁጥር አንድ ብቻ የነበረውን የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ለማስፋፋት በያዘው ዕቅድ በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሶስት ትምህርት ቤቶችን ለመከፈት እንቅስቃሴ ጀምሮ ዕቅዱን በማሳካት በያዝነው ሳምንት ሁለተኛውን ትምህርት ቤት በአረካ ከተማ አስተዳደር በይፋ ስራ ማስጀመሩ ይታወሳል፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ በቦዲቲ ከተማ አስተዳደር በዞኑ ሶስተኛውን የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በይፋ ስራ አስጀምሯል፡፡ በማስጀመሪያው ስነስርዓት የተገኙት የልማት ማህበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና በዞኑ ስራ እየጀመሩ ያሉ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶች ልክ እንደወላይታ ሶዶ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ውጤታማ እንዲሆኑ ልማት ማህበሩ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ልማት ማህበሩ የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶችን በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፋት የያዘውን ዕቅድ እንዲያሳካ ህብረተሰቡና የዞኑ አስተዳደር እያደረገ ስላለውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ ማስጀመሪያ ስነስርዓት የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ዳንኤል ደሌን ጨምሮ ሌሎች የዞኑና የቦዲቲ ከተማ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ማህበሩ በትናንትናው ዕለት ሁለተኛውን የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በአረካ ከተማ ስራ ያስጀመረ ሲሆን የፊታችን ዓርብ ዕለት ደግሞ በገሱባ ከተማ አስተዳደር አራተኛውን ስራ የሚያስጀምር ይሆናል፡፡