በተለያዩ አካባቢዎች የልማት ስራዎችን እየጎበኘ ያለዉና በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የተመራዉ ልዑካን ቡድን በወላይታ ሶዶ ከተማ ተገኝተዉ የተሞክሮ ማዕከል የሆነዉን ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ጎብኝቷል።
ልዑካን ቡድኑ በትምህርት ቤቱ ያለዉን የመማር ማስተማርና ሌሎች ተግባራትን በወላይታ ልማት ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሰፋ ናና ማብራሪያ ተሰጥቶታል ። ዶ/ር መቅደስ በጉብኝቱ የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች በክፍሎች፣ በቤተሙከራና አይ ሲ ቲ ክፍሎች ተዘዋውረው አበረታትተዋቸዋል፡፡
ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በ2000 ዓ.ም የተቋቋመ፣ በወላይታ ልማት ማህበር የሚተዳደርና ብሩህ አዕምሮ እያላቸው በተለያዩ ምክንያቶች ጥራት ያለውን ትምህርት ማግኘት ያልቻሉ ተማሪዎችን በመቀበል ጥራት ያለውን ትምህርት ይሰጣል፡፡
ትምህርት ቤቱ በባለፉት ጊዜያት በክልላዊና ብሔራዊ ፈተናዎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ስመ ጥር የሆኑ ተማሪዎችን በማፍራት በርካታ የህክምና ደክተሮችንና በተለያዩ ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ማፍራቱ የሚታወቅ ነው፡፡ እንዲሁም ተማሪዎች ከሀገር አልፈው በዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር በላቀ ውጤት ትምህርታቸውን ተከታትለው በማጠናቀቅ በውጭ ሀገራት በስራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ላለፉት 17 ዓመታት ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚመጡና መልካም ተሞክሮና ልምድ ለሚፈልጉ አካላት የተሞክሮ ማዕከል መሆኑ ይታወቃል።







