በወላይታ ልማት ማህበር የሚተዳደረው የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ብቻ ሀኖ በአገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር ሆኖ ውጤታማ ተማሪዎችን እያፈራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ማህበሩ በያዝነው 2017 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቱን ቁጥር በመጨመር በዞኑ ሶስት አካባቢዎች በይፋ ስራ አስጀምሯል፡፡
በዛሬው ዕለት አራተኛው የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በገሱባ ከተማ አስተዳደር በይፋ ስራ ጀምሯል፡፡ በስራ ማስጀመሪያው መርሃ ግብር የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ የክልሉ መንግስት ለዚህ ውጤታማ ለሆነው የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት ድጋፍ እንደሚያደርግ በክልሉ መንግስት ስም ቃል በመግባት ትምህርት ቤቱ ተደራሽነቱን በማስፋት በገሱባ ከተማ ስራ በመጀመሩ ለከተማውና አጎራባች ወረዳዎች አንኳን ደስ አላችሁ በማለት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡
የወላይታ ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና በበኩላቸው ልማት ማህበሩ የገሱባ ወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤትን ጨምሮ አሁን በዞኑ የተከፈቱ ሶስቱም የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤቶች በወላይታ ሶዶ ወላይታ ሊቃ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረው ትምህርት ቤቶቹ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ የሆኑ ተማሪዎችን እንዲያፈሩ የተለመደውን ጠንካራ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በስፍራዉ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያምን ጨምሮ የገሱባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ሰራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።