የወላይታ ልማት ማህበር (ወልማ) 24ኛ ዓመት መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን እያካሄደ ነው።
ጉባኤውን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የማህበሩ የበላይ ጠባቂ አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያም የወላይታ ልማት ማህበር ባለፉት 24 ዓመታት በግብርና በሥራ ዕድል ፈጠራ በጤና በንፁህ መጠጥ ውሃ እና በመሠረተ ልማት ሥራዎች ለዞኑ ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያላቸው በርካታ ተግባራት ተፈጽመዋል ብለዋል።
የህዝባችን ፍሬ የሆነው የሊቃ ትምህርት ቤት ወደ ልህቀት ማዕከልነት እንዲያድግ በተደረገው ንቅናቄ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በክላስተሮች የሊቃ አቻ የሆኑ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ጴጥሮስ መሰል ትምህርት ቤቶችን ለማዳረስ ልማት ማህበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት የዞኑ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በልማት ማህበሩ ስም የተቋቋሙ የገቢ ማስገኛ ተቋማትን ለማጠናከርም ዞኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ ጴጥሮስ ተናግረዋል።
ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለሚደረገው ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለው የልማት ማህበሩ እርሻ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያብራሩት ዋና አስተዳዳሪው ለማህበሩ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ በዞኑ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢፌዴሪ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታና የወላይታ ልማት ማህበር ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር እንድሪያስ ጌታ የልማት ማህበሩ በሰብአዊ ልማት፣ በጤና፣ በዘላቂ ልማትና ኑሮ ማሻሻያ ዘርፍ ሥራዎች አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በግብርናም ዘርፍ ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ ተግባራት፣ በአካባቢ ጥበቃና በአማራጭ የገቢ ማግኛ ዘርፍ በርካታ ተግባራት ታቅደው መፈጸማቸውንም ዶክተር እንድርያስ ጌታ አንስተዋል።
ልጆቻችን ጥራት ያለው ትምህርት በማግኘት ተወዳዳሪ ዜጎች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቷል ያሉት ሊቃ ትምህርት ቤት ለዚህ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ማህበሩ ከአባላት በሚሰበሰብ እና ከተለያዩ ምንጮች በሚያገኘው ገቢ በመሆኑ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የሚሰበሰበው ሀብት ከታቀደው ዕቅድ አንጻር እና ከልማት ፍላጎት አንጻር እጅግ አነስተኛ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ዶክተር እንድሪያስ።
የወላይታ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሰፋ ናና ልማት ማህበሩ ባለፉት 24 ዓመታት የህዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ሰው ተኮር ልማትና ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራሞች በመንደፍ በርካታ ተግባራት የተፈጸሙ ሲሆን ለዞኑ ብሎም ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።
አቶ አሰፋ አክለውም ልማት ማህበሩ የጀመራቸው ፕሮጀክቶች ቢጠናቀቁ ለበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጠቀሜታ የሚሰጡ በመሆናቸው ሁሉም ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በጉባኤው የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የወረዳና ከተማ አስተዳደሮች አመራሮች፣ የልማት ማህበሩ አመራር ቦርድ አባላት፣ አጋሮችና አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።










